የጤና ጣቢያዉ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልእክት

እንኳን ወደ ጤና ጣቢያችን በደህና መጡ። የጤና ትቋማችን ዋና ተልዕኮ ማዕከል ያደረገው “ወደ ጤና ጣቢያችን የሚመጣ እያንዳንዱ ተገልጋይ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ አክብሮት የተመላበት እና ከፍተኛ ጥራት ያለው እንክብካቤ ይገባዋል” የሚል ጽኑ የቃልኪዳን መሰረት ላይ ነው። በኢትዮጵያ የጤና ጣቢያ ሪፎርም እና በሃገር ዓቀፍ የጤና ተቋማት የአገልግሎት ደረጃዎች መስፈርቶችን አሟልተን አገልግሎት የምንሰጥ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ተቋም እንደመሆናችን፣ ለማህበረሰባችን ተደራሽ፣ ውጤታማ እና በፍላጎታቸው ላይ የተመሠረተ አገልግሎት ለመስጠት ሳናሳልስ እንተጋለን።

ራዕያችን ከፍተኛ የህክምና አገልግሎት ጥራት፣ የታካሚ ደህንነት፣ ተጠያቂነት እና ርኅራኄ የተላበሰ የጤና ማዕከል መገንባት ነው። አገልግሎቶቻችንን በማስረጃ ላይ ተመስርቶ በሚሰጥ እንክብካቤ (evidence-based care)፣ ተከታታይነት ባለው የሙያተኞች የሙያ ማጎልበቻ ፕሮግራም (ሲፒዲ)፣ የተሻሻለ የላቦራቶሪ እና የምርመራ አገልግሎቶች እና እንደ ኤሌክትሮኒክ የሕክምና መዝገቦች (ኢ.ኤም.አር) እና ሌሎች ዘመኑን የዋጁ የጤና ቴክኖሎጂዎችን በማጣመር እያጠናከርን እንገኛለን። በተጨማሪም ተገልጋዮች ባጠረ የጥበቃ ጊዜ አገልግሎት የሚያገኙበት፣ የተሻለ የእንክብካቤ ቅንጅት ያለበት እና የሚስብ የስራ አካባቢን እንዲያገኙ የሚረዱ የአሰራር ስርዓቶቻችንን በተከታታይነት እየገመገምን እያሻሻልን ነው።

ሁሉም የተቋማችን አገልጋዮች የስኬታችን ቁልፍ መሠረቶች ናቸው። የጤና ባለሙያዎችና ሌሎች ደጋፍ ሰጭ አገልጋዮቻችን በሙያና ስነ ምግባር እንዲጎለብቱ፣ እርስበርስ እንዲተባበሩ እና አዳዲስ ሀሳቦችን እንዲያፈልቁ የሚያበረታታ የስራ አካባቢ ለመፍጠር ቁርጠኞች ነን። በስራ አመራር ልማት፣ በስራ ቦታ ድጋፍ እና ተከታታየነት ባላቸው የሙያ ማጎልበቻ ስልጠናዎች አማካኝነት ማህበረሰባችን የሚገባውን የእንክብካቤ ደረጃ ማቅረብ የሚችል ተነሳሽነት ያለው የጤና ሰው ሃብት ለመገንባት ተግተን እንሰራለን። በተጨማሪም ጤና ጣቢያችን የማህበረሰቡ ክፍልና ሃብት ነው። ስለሆነም የማህበረሰቡን የጤና ፍላጎቶችን ለመረዳት፣ በሽታን ለመከላከልና ጤናን ለማበለጸግ፣ እና ወሳኝ የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ከማህበረሰብ አባላት፣ ከሃገር በቀል ድርጅቶች እና ከሌሎች ጤና አጋሮቻችን ጋር በንቃትና በቅርበት እንሰራለን። እንደዚህ አይነት ጠንካራ ሽርክናዎች አዳዲስ ለሚከሰቱ የጤና ችግሮች የበለጠ ውጤታማ በሆነ መንገድ ምላሽ እንድንሰጥ እና የአገልግሎት ጥራታችንን እንድናሻሽል ያስችሉናል።

በመረጃ፣ በግልጽነት እና በኃላፊነት የተመራ የሀብት አስተዳደር በመመራት አፈጻጸማችንን በተከታታይንት በመለካትና ማስረጃን በመጠቀም ውሳኔዎቻችንን እናሻሽላለን። ይህም አሰራር አገልግሎቶቻችን ዘላቂ፣ ተጠያቂ እና የማህበረሰባቸንን ተለዋዋጭ ፍላጎቶች የሚመልሱ እንዲሆኑ ያረጋግጣል። እንደ ዋና ስራ አስኪያጅ የእኔ ቁርጠኝነት ተቋሜን በታማኝነት መምራት፣ የልህቀት ባህልን ማበረታታት እና የጤና ጣቢያችንን ለእንክብካቤ፣ ለፈውስ እና ለተስፋ የሚታመን ቦታ ሆኖ እንዲቀጥል ማረጋገጥ ነው። ከታማኝና ትጉህ አገልጋዮቻችን፣ ከአጋሮቻችን እና ከማህበረሰባችን ጋር በመተባበር የመጀመሪያ ደረጃ ጤና አገልግሎትን እያጠናከርን “ጤናማ ዜጎች እና የበለጸገች ሃገርን” ለመገንባት ተግተን እንሰራለን። ለአገልግሎት ስለመረጡንና በእኛም ስለተማመኑ ከልብ እናመሰግናለን።

ዶ/ር ለምለም ሞላ , በልደታ ክ/ከተማ የጄነራል ጃጋማ ኬሎ መታሰቢያ ጤና ጣቢያ ዋና ሥራ አስኪያጅ
image description